የተዘናጋንበት የሚመስለው የኤች አይቪ ጉዳይ ….

ባለፉት አመታት እንደ ሀገር ኤች አይቪ ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የተመዘገበው ውጤት በመንግስትና በህብረተሰቡ ውስጥ መዘናጋትን በመፍጠሩ የበሽታው ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለፀ።

አለማችን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት መገባደድ በኋላ ትልቅ ስጋቶች ተጋርጠውበታል።

የመጀመሪያው በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ምክንያት የሚጠፋው የሰው ልጅ ቁጥር መብዛት ፣ በተለያዩ ሀገራት የሚፈፀሙ የሽብር አደጋዎችና መድሀኒት የለሽ በሽታዎች መከሰት በብዛት አምራች የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል በዚሁ የሚጠፋው የሰው ልጅ ህይወት ትልቅ ስጋቶች ሆነዋል።

ከሁሉም በላይ ግን በተለይ በባለፉት ሦስት አስር አመታት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው እየገደለና መድሀኒትና ክትባት የታጣለት ፣ የሀገራትን ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እያስከተለ ያለ በተለይ በድህነትና በዝቅተኛ ኢኮኖሚ ውስጥ ያሉ ሀገራትን ዳዴ እያስባለ የሚገኘው በሽታ ኤች አይ ቪ /ኤድስ ሆኗል።

የቤንች ሸኮ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ምናሴ እንደገለፁት ኤች አይ ቪ ኤድስ በተለይ አምራችና ነገ ሀገር ተረካቢ የሆነውን ወጣት ትውልድ በመጉዳት የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ በመንግስት የተለያዩ የመከላከያና የመቆጣጠሪያ ስልት ተነድፎ እንደ ሀገር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ኤች አይቪ ኤድስን በመከላከልና መቆጣጠር ሥራ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን ከዚህም አንዱ በሆነው ኤች አይቪ ኤድስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በ2016 በጀት ዓመት 9 ወራት 79 ተጋላጭ ህፃናት የዲቢኤስ ምርመራ በ12 ወራት ዕድሜያቸው ውስጥ የኤች አይቪ ምርመራ ያገኙ ሲሆን የተመረመሩት ህፃናት ሙሉ በሙሉ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን አቶ ኤሊያስ ጠቁመዋል ።

በዞኑ ጤና መምሪያ የዘርፈ ብዙ ኤች አይ ቪ /ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ዳንኤል ዚያብ እንደገለፁት የተባበሩት መንግስታት የኤድስ መቆጣጠሪያ ድርጅትን መረጃ ዋቢ አድርገው እንዳሉት በአለማችን ባለፉት ሦስት አስርት አመታት ውስጥ ከ39 ሚሊየን በላይ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ይገኛል።

የስርጭቱ ምጣኔ ከክልል ክልል፣ ከአንድ ቦታ ሌላ ቦታ፣ በተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም በከተማና በገጠር በከፍተኛ ደረጃ የሚለያይና
አዳዲስ በኤችአይቪ የመያዝ ምጣኔ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚፈለገው መጠን እየቀነሰ እንዳልሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

ይበልጥ ተጋላጭ የማበረሰብ ክፍሎች የስርጭት ምጣኔ ከአጠቃላይ ማህበረሰቡ የስርጭት ምጣኔ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ቅርብ የተጠናው ጥናት እንደሚያሳየው የሴተኛ አዳሪዎች (18 %) በላይ መሆኑን ያሳያል ፡፡

የአፍላዎችና ወጣቶች ለኤችአይቪ ያላቸው ተጋላጭነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱና የችግሩ ስፋት ከፍተኛ እንደሆነ ሌላው ማሳያ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አዲስ በኤችአይቪ የመያዝ ምጣኔን ለመቀነስ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ መተላለፍን መከላከል ሲሆን አፈጸጸሙ ዝቅተኛ መሆኑ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አለመቻሉን ያሳያል፡፡

ቫይረሱ በደማቸው ከተገኘባቸው ሰዎች 3.2 ሚሊዮን በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን አልፏል ።
በአሁኑ ሰዓት 39 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በየአመቱ 1.3 ሚሊየን በላይ ሰዎች አዲስ በቫይረሱ ይያዛሉ።

በየዓመቱ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ካሉ ወገኖች ውስጥ ከ630 ሺህ በላይ ሰዎች በአማካይ ህይወታቸውን እንደሚያጡ አስተባባሪው ጠቁመዋል።

በሀገራችንም አሁን ላይ 690 ሺህ የሚሆኑ ወገኖች በቫይረሱ መያዛቸውን አቶ ዳንኤል ጠቁመው እንደ ሀገር የቫይረሱ ስርጭት 0.9 % ደርሷል ብለዋል።

ይህ አሀዝም የተባበሩት መንግስታት አንድ ሀገር በቫይረሱ ወረርሽኝ ውስጥ ለመሆን አንድና ከአንድ በመቶ በላይ መሆን አለበት በሚለው መስፈርት መሰረት ሀገራችን በኤች አይ ቪ / ኤድስ ወረርሽኝ ከተያዙ ሀገራት ምድብ ውስጥ ሊካተት 0.1%, የቀረው በመሆኑ ወረርሽኝ ለመሆኑ እጅግ የተቃረበ መሆኑን ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ ስርጭቱ ከክልል ክልል ፣ ከዞን ዞንና ከወረዳ ወረዳ የተለያየ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ቤንች ሸኮ ዞን የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበትም ጊዜ የነበረ ሲሆን በዚህም ህይወት መጥፋት ፣ ለቤተሰብ መፍረስና ህፃናት ያለ አሳዳጊ ሜዳ ላይ እንዲቀሩም ያደረገበት ጊዜም ነበር።

ይሁን እንጂ ባለፉት አመታት በተገኘው ውጤት እንደ ሀገር መዘናጋትን ፈጥሯል ያሉት አስተባባሪው ይህም መዘናጋት በዞናችንም የሚታይ ነው ብለዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በ2016 ዓ.ም በወጣው መረጃ መሰረት 8 ሺህ 730 ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ይገኛል።

በቤንች ሸኮ ዞን በ2016 ዓ.ም በተወሰደው መረጃ 3 ሺህ 443 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ታውቋል።

ከነዚህ ውስጥ 3 ሺህ 227 የሚሆኑት አዋቂዎች ሲሆኑ ቀሪው 219 የሚሆኑት ከ15 ዓመት በታች ህፃናት መሆናቸውን መረጃው ያሳያል።

በመረጃው መሰረት ከ 3 ሺህ 227 አዋቂዎች ውስጥ 1ሺህ 969 ወይም 61 % የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ደግሞ ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው አቶ ዳንኤል ገልፀዋል።

በወረዳ እና በከተማ አስተዳደር ደረጃ ስርጭቱ ሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር 2.05 % ፣ ጉራፈርዳ 0.72% ፣ ደቡብ ቤንች 0.71%፣ ሼይቤንች 0.67% ፣ ሲዝ ከተማ አስተዳደር 0.66%፣ ሸኮ 0.34 ፣ እና ጊዲቤንች 0.01% የደረሰ ሲሆን ሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር መረርሽኝ ውስጥ ያለ መሆኑን መረጃው ያመላክታል።

በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ሕግ መሰረት ይላሉ አቶ ዳንኤል፤ ከአጠቃላይ ሕዝቡ ከአንድ በመቶ በላይ በበሽታው ከተያዘ እንደ ወረርሽኝ እንደሚቆጠር ጠቁመው በዞኑ ሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ወረርሽኝ ውስጥ እንዳለ መረጃው ያሳያል ብለዋል።

ሚዛን አማን ከተማ ከፍተኛ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት ካለበት ጋምቤላ ክልል ወደ ከተማዋ ፍሰት ያለባት በመሆኑ ፣ከፍተኛ የሆነ የሴተኛ አዳሬዎች መኖር፣ ከተማው ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያለበት በመሆኑ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ ሰዎች ማረፊያ መሆኗ የስርጭቱ መጠን ወደ ወረርሽኝ እንዲደርስ ማድረጉን አቶ ዳንኤል ገልፀዋል።

በዞኑ ይበልጥ ተጋላጭ የማበረሰብ ክፍሎችየስርጭት ምጣኔ ሲታይ ሴተኛ አዳሪዎች፣ የቀን ሠራተኞች ፣ቫይረሱ በደማቸው የሚገኙ አጋሮች፣ቫይረሱ በደማቸው ከለባቸው ወላጆች የተወለዱ ልጆች፣ ወላጅ አጥ ህፃናት፣ መሆናቸው ተጠቁሟል።

አዳዲስ በኤች አይ ቪ በደማቸው የተገኘባቸው ሁሉም ህክምናውን እንዲጀምሩ የተደረገ ሲሆን
በአሁኑ ጊዜ በ8 የጸረ-ኤች አይ ቪ ኤድስ ህክምና በሚሰጥባቸው ተቋማት ህክመናቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ናቸው።

ከነዚህ ውስጥ የበሽታው/የቫይረሱ ጫና የቀነሰላቸውን ለመለየትና የህክምና አገልግሎቱን ውጤታማነት ለመለካት ናሙና የተላከላቸው መሆኑ ተገልጿል።

አቶ ኤሊያስ እንደገለፁት አሁን ላይ እንደ ዞን የሚታየውን የስርጭት መጠን ለመቀነስና ለመቆጣጠር በቅድሚያ ሁሉም የዞኑ ነዋሪ በመመርመር ራሱን ማወቅ እንዳለበት ገልፀው በመቀጠልም በሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶችና በግል ድርጅቶች ውስጥ የስራው አንድ አካል አድርጎ በመውሰድ የማህበረሰብ ውይይት ማድረግ ይገባል።

ቫይረሱ በደማቸው ለተገኘባቸው ወገኖች ድጋፍና እንክብካቤ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል።

አቶ ኤሊያስ አክለውም ኤች አይቪ ኤድስ የተረሳ የመሰለና ትኩረት የቀነሰ ቢመስልም የስርጭቱ ምጣኔ ወደ ወረርሽኝ የተቃረበ በመሆኑ ሁሉም ሠው ራሱንም፣ ቤተሰቦቹን፣ ጎረቤቶቹንና የአካባቢውን ማህበረሰብ ከኤች አይቪ ኤድስ እንዲጠብቅ ጥሪ ቀርቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back To Top