የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል

የሸኮ ብሔረሰብ ለዘመናት የቆየ የመተሳሰብ ፣ የአብሮነትና የአንድነት ታሪክ ያለውና የውብ ባህልና እሴቶች ባለቤት ነው።

ህዝቡ ለዘመናት ጠብቆ ፣ ተንከባክቦና ሳይበረዝ ያቆያቸው ቱባ ባህሎች ፣ ወግና አኩሪ እሴቶች ያሉት ሲሆን ለቀጣዩ ትውልድም ለማስተላፍ እየተሰራ ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው።

ከነዚህ ውብ ፣ ማራኪና ትልቅ እሴት ከሚታይባቸው ባህላዊ ክዋኔዎች አንዱና ዋነኛው “ቲከሻ ቤንጊ” የሸኮ ህዝብ የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል ተጠቃሽ ነው።

“ቲከሻ ቤንጊ” ለሸኮ ህዝብ ከዘመን መለወጫ ትውፊታዊ በዓልነቱ ባሻገር ድርብ ድርብርብ መልዕክትና እሴቶችን የያዘ ነው።

ወርሀ ጥር ለሸኮ ህዝብ የአዲስ አመት ፣ የአዲስ ተስፋ ፣ የአዲስ ብስራትና ለመጪው አመት በሰላምና በጤና ጠብቆ እንዲያቆያቸው በጋራ ተሰባስበው ለፈጣሪያቸው ምስጋና የሚያቀርቡበት ወቅትም ነው። ወርሀ ጥርና የግራዋ ተክል ደግሞ በብሔረሰቡ ዘንድ ትልቅ ቁርኝትና ተምሳሌት ያላቸውም ናቸው።

“ቲከሻ ቤንጊ” ወይም የሸኮ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ ቀን በብሔረሰቡ የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ሲሆን የህዝብ ለህዝብ መገናኛና ትስስሩን ለማጠናከር ከሚጠቀሙበት እሴቶቻቸው አንዱ በመሆኑ በድምቀት የሚከበር በአል ነው።

የለውጡ መንግስት እንደዚህ አይነት ቱባ የህዝቦች የማንነት መገለጫና እሴቶችን ለማልማት ፣ ለማስተዋወቅ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

የሸኮ ህዝብ ለዘመናት ተፈጥሮን እንደነበረ ጠብቆና ተንከባክቦ ያቆየበት ባህሉ በተገቢው ሊጠናና ተሞክሮ የሚቀመርበት ነው። በሀገራችን “የኢትዮጵያ ሳንባ” ተብለው ከሚጠቀሱ አካባቢዎችም የቤንች ሸኮ ዞን አንዱና ተጠቃሽ ነው። ይህ ልምድ ዝም ተብሎ የተገኘ ሳይሆን የህዝቦች ለተፈጥሮ የሰጡት አዎንታዊ ምላሽ ማሳያና ጥበብም ጭምር ነው።

የቤንች ሸኮ ዞን ህዝቦችም ለዘመናት የቆዩ የውብ ባህል ፣ ታሪክና እሴቶች ባለቤት ሲሆን እነዚህን ለማስፋት ፣ ለማስተዋወቅና ለአዲሱ ትውልድ ለማስተላፍም ባለፉት አመታት ሁለት ዙር የዞኑ የባህል ፣ ቋንቋና ታሪክ ሲምፖዚየም አዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን ይህን በተገቢው መንገድ ሳይቆራረጥ ማስቀጠል ያስፈልጋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በቀጣይ ከሸኮ የዘመን መለወጫ “ቲካሽ ቤንጊ” በዓል ከተከቨረ በኋላ የቤንች ብሔረሰብ በዓል በቅርቡ የሚከበር ሲሆን በቀጣይ በሁለቱ ታላላቅ በአላት በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መልዕክቴን ማስተላለፍ እወዳለሁ።

ለመላው የዞናችን ነዋሪዎች በድጋሚ እንኳን ለሸኮ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል “ቲከሻ ቤንጊ” በሰላምና በጤና አደራሳችሁ እያልኩ ይህንን ታሪካዊ በዓል ላዘጋጁ ፣ ላስተባበሩና ለመሩ አካላት በሙሉ በዞኑ መንግስትና በራሴ ስም ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ። አመሰግናለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back To Top