የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው። አቶ ሀብታሙ ካፍቲን

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን የሚዛን አማን ከተማ አየር ማረፊያ ግንባታ በተመለከተ ለሚዲያዎች መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ለሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ከሚያስፈልገው መሬት ውስጥ 1 መቶ 27 ሄክታሩ የካሳ ክፍያ ተጠናቋል።

የአውሮፕላን ማረፊያው ለዞናችን ብሎም ለሀገሪቱ ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንፃር የዞኑ መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

ግንባታው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ቦታውን ከይገባኛል ጥያቄ ነፃ ለማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀው ለግንባታው ከሚያስፈልገው 2 መቶ 53 ሄክታር ቦታ 1 መቶ 27 ሄክታሩን ካሳ በመክፈል ከይገባኛል ነፃ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ለካሳ ክፍያ ከሚያስፈልገው 300 ሚሊዮን ብር በበጀት አመቱ ብቻ ከ98 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ መከፈሉን አቶ ሀብታሙ ካፍቲን ገልፀዋል።

ተለዋጭ የቤት ቦታ ለሚያስፈልጋቸው 5 መቶ 29 አባወራዎችና እማወራዎች ውስጥ ለ 1 መቶ 68ቱ ብቻ የተሰጠ መሆኑንና ገና ቀሪ 3 መቶ 61 አባወራዎችና እማወራዎች ተለዋጭ ቦታ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

አክለውም ጥናት ካልተደረገላቸው ውጪ ቀሪ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የሚከፈል የካሳ ክፍያ መኖሩን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው ቀሪው ዞኑ ካለው የበጀት እጥረት አንፃር የፌዴራል፣ የክልልና የዞን የህብረተሰብ ክፍልና የመንግስት ሰራተኛው የተጠናከረ ድጋፍ በማድረግ ከዞኑ ህዝብና መንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ አስተላልፈዋል።

ዋና አስተዳዳሪው አክለውም ለልማት ተነሺዎች የሚከፈለውን የካሳ ገንዘብ የዞኑ ህዝብና የመንግስት ሰራተኞች ከመጀመሪያው እስካሁን ድረስ እያደረጉ ላሉት ድጋፍ አመስግነው በቀጣይ ላልተነሱ እማወራዎችና አባወራዎች የሚደረገው ድጋፍ በተጀመረው ልክ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል።

የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፍያ መሰረት ድንጋይ ሰኔ 13/2013 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ መቀመጡ ይታወሳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back To Top