ከ8 ሺ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የካሹ መስኖ ግድብ ግንባታ ጥናት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ተካሄደ።

በቤንች ሸኮ ዞን ሼይ ቤንችና ደቡብ ቤንች ወረዳ መሀል የካሹ ወንዝ ላይ የሚገነባው የመስኖ ግድብ ጥናት አስመልክቶ ከሁለቱ ወረዳ የሚመለከታቸው አካላት ጋር የምምክር መድረክ ተካሄዷል።

በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ስራዎች ኮርፖሬሽን አማካኝነት የሚጠናው ይህ ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ተጠንቶ እንዲጠናቀቅ ያስችል ዘንድ አጠቃላይ የጥናት ስራውን አስመልክቶ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን ሀገራችን በርካታ የውሃ ሀብት ባለቤት ብትሆን በዝናብ ጥገኝነት ያልተላቀቅን በመሆናችን የምግብ ዋስትናን በበቂ ሁኔታ ማረጋገጥ አልተቻለም ብለዋል።

ያለንን የውሃ ሀብት ለመጠቀም የመስኖ ተቋማትንን በመገንባት በአመት አንዴ የሚያመርተውን አርሶአደር ሶስቴ እንዲያመርት መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ያደጉ ሀገራት ያላቸውን መሬት በትንሽ የውሃ ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም የተሻለ የምግብ ዋስትተናን እያረጋገጡ እንደሚገኙ ጠቁመው እነዚህን ተሞክሮዎች ወደ ሀገራችን በማምጣት የተጀመሩ የመስኖ ግንባታዎችን በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ ቀጣይ ትኩረት አድርገን መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

ኢንጂነር አሸናፊ ሽብሬ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመስኖ ተቋማት አስተዳደርና ልማት ኤጀንሲ ዳይሬክተር በበኩላቸው በክልሉ በርካታ የመስኖ ተቋማት እየተገነቡ መሆናቸውን ገልፀው የካሹ መስኖ ግድብ አንዱ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ተጠንቶ ወደስራ እንዲገባ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ወልደየስ ዘለቀ በበኩላቸው የካሹ መስኖ ግድብ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከ8 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዌል።

አያይዘውም በ4 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የሚሸፍነው ይህ ግድብ ከሼይ ቤንች ወረዳ 4 ቀበሌዎችን እና ከደቡብ ቤንች ወረዳ 2 ቀበሌዎች እንደሚካተቱም አብራርተዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች የሁለቱ ወረዳ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back To Top