ርዕሳነ መስተዳድሮች ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) የፋኦን አግሪኮላ ሜዳልያ በመሸለማቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ


የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ በመሸለማቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ሽልማቱ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ የሚያደርግ እና የላቀ ገፅታዋን የሚያሳድግ በመሆኑ ላበረከቱት አስተዋጽዖም እናመሠግናለን ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት÷ ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሠሯቸው መልካም ሥራዎች ጎልተው የሚታዩ መሆናቸን ያመላከተ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

ይህ ሁኔታ ዓለም ላይ የምንታወቅበትን የድህነት ታሪክ እየቀየረ ያለ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማሳያ ነው ብለዋል።

እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት÷ እረፍት የለሹ፣ ለኢትዮጵያ ጊዜያዊ ችግር ፍቱን መፍትሄ ሃሳብ አፍላቅ መሪያችን ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በሳል አመራር ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም የጋምቤላ ክልል÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ባደረጉት ዘርፈ ብዙ ስራ ውጤት በመመዝገቡና ተሸላሚ በመሆናቸው የክልሉ መንግስትና ሕዝብ ኩራት ይሰማዋል ብሏል።

በቀጣይም ዘርፉን ለማሳደግና የሕዝቦችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የክልሉ መንግስትና ሕዝብ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሳል አመራር ጋር በጋራ እንደሚሰራ ገልጿል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back To Top