“መስዋዕትነት ለብሔራዊ ክብር ፣ ለነጻነት እና ለሉአላዊነት” በሚል መሪ ቃል ጳጉሜ 2 የመስዋዕትነት ቀን በሚዛን አማን ተከበረ።

“መስዋዕትነት ለብሔራዊ ክብር ፣ ለነጻነት እና ለሉአላዊነት” በሚል መሪ ቃል ጳጉሜ 2 የመስዋዕትነት ቀን በሚዛን አማን ተከበረ።

ሚዛን አማን ፣ ጳጉሜ 2/2015 ቀኑን የፌደራል ፖሊስ ፣ የማረሚያ ፣ የዞን ፣ የከተማ ፖሊስና በጸጥታ መዋቅሩ አባላት በፓናል ውይይት ተከብሯል።

የቤንች ሸኮ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ኮጁ ባደከች ጳጉሜ 2 የመስዋዕትነት ቀንን አስመልክቶ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሁፍ ኢትዮጵያ ከየትኛውም ሀገር በላይ ለዳር ድንበሯ መጠበቅ ፣ ለሉዓላዊነቷ መከበር ከጥንት እስከ ዛሬ ጀግና ልጆቿ ለህይወታቸው ሳይሳሱ መስዋዕትነት ከፍለው የገነቧት ሀገር ናት ብለዋል።

በአድዋ ፣ በተምቤን ፣ በማይጨው ፣ በወልወልና በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከወራሪ ጣሊያኖች ጋር ፤ በዶጋሊ ፣ በጉንደትና በጉራ ከግብጾች ጋር ፤ በመተማ ከሱዳኖች ፤ በአፋር ምድር ከቱርኮች ፤ በካራማራ ከሶማሊያ ፤ በባድመ ከኤርትራ ጋር የተደረጉ ጦርነቶች ከውጭ ሀገራት ጠላቶቻችንንና ወራሪዎች ጋር የተደረጉ ጦርነቶች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

የአሁኑ ትውልድ መስዋዕትነትን የሚከፍል ብቻ ሳይሆን መጪውን ሀገር ተረካቢ ትውልድ በመቅረጽ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የኢትዮጵያዊያንን የመስዋዕትነት ፣ የአሸናፊነት እና የጀግንነት እሴት በኩራት እንዲዘክር እና እንዲረከብ ለማድረግ ወጣቱን ማስገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ ዞን ባለፉት አመታት በተለያዩ ወረዳዎች የነበረውን የጸጥታ መደፍረስ የጸጥታ መዋቅሩ መስዋዕትነትን ከፍሎ የመጣው ለውጥ የሚደነቅ ነው ብለዋል። በሂደቱም በርካታ ጸረ ሰላም ኃይሎች ለጸጥታ መዋቅሩ እጃቸውን የሰጡ ሲሆን አሻፈረኝ ያሉት ላይ እርምጃ መወሰዱንም ገልጸዋል።

በመድረኩ ተሳታፊ የፀጥታ መዋቅሩ አባላትና አመራሮች እንደተናገሩት ሀገር ውስጣዊ ሰላሟንና የውጭ ወራሪ ኃይሎችን በጽናትና በታማኝነት ማገልገል ከሰራዊቱ የሚጠበቅ ቀዳሚ ተግባር ነው ብለዋል። የጸጥታ መዋቅሩ የተሻለችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ዶክተር ካሳ እንደተናገሩት አዲሱ ትውልድ በጀግኖች አባቶች የተከፈለለትን መስዋዕትነት በአግባቡ አውቆ ሊዘክርና ተተኪ ሊሆን ይገባል ብለዋል። አዲሲቷን ኢትዮጵያ የመረከብና የማጽናት ኃላፊነት ለተወጣቱ የተሰጠ ትልቅ ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል።

የጸጥታ መዋቅሩም መስዋዕትነት ከራስ በላይ ለህዝብ ራስን አሳልፎ መስጠትና ለሰላም ዘብ መቆም መሆኑን ጠንቅቆ በማወቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። የጸጥታ መዋቅሩ የተግባርና የአመለካከት አንድነትን ይዞ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ኮጁ ባደከች በመድረኩ ማጠቃለያ እንደተናገሩት በሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ የፀጥታ መዋቅሩ ሚና የጎላ ነው ሲሉ ገልፀዋል። ዛሬ ላይ በዞናችን በአብዛኛው መዋቅሮች የመጣው ሰላም በጸጥታ መዋቅሩ መስዋዕትነትና ትልቅ ዋጋ ተከፍሎበት የመጣ ነው ብለዋል።

ትውልዱም ይህን መስዋዕትነት በአግባቡ ሊገነዘብና በሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል።

በተዘራ ጥላሁን

ለበለጠ መረጃ ፦
ድረ ገጽ፦ www.benchshekozonecom.gov.et
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/benchshekozonepublicrelationoffice
ዩትዩብ፦ https://youtube.com/@BenchShekoZoneGovernmentCommun?feature=share8
ቴሌግራም፦ https://t.me/bszgca
ትዊተር፦ https://twitter.com/BenchGov?t=V1DGL3YnPHirGEiTq-jh2A&s=09
ኢንስታግራም፦ https://instagram.com/benchshekozonepr?utm_source=qr&igshid=MzNlNGNkZWQ4Mg%3D%3D
ቲክቶክ፦ tiktok.com/@benchshekozonegov
በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back To Top